በ2 ወር ውስጥ 101 ሕጻናት ተደፍረዋል!
በ2 ወር ውስጥ 101 ሕጻናት ተደፍረዋል!
ኮሮና ወደ ሀገራችን ከገባ በኅላ ሌላ ገጽታ እያሳየን ይገኛል። ብዙዎች በቤታቸው እንዲቀመጡ በሚመከርበት ወቅት በቤት ውስጥ በሕጻናትና ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ልብ ሊባል እንደሚገባ ከምንሰማቸው አንዳንድ መረጃዎች መገንዘብ ይቻላል።
በትላንትናው ዕለት በዋልታ ቴሌቪዥን ’51 በመቶ’ በሚል በተዘጋጀ ዝግጅት ላይ የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አልማዝ አብርሃ እንደገለጹት ከ3 ሆስፒታሎች በተገኘ ሪፓርት ብቻ በሁለት ወር 101 ሕጻናት መደፈራቸውን ገልጸዋል።
ይህ ቁጥር ትምህርት ቤቶች በተዘጉበት ፣ ሕጻናት ከቤት በማይወጡበትና ጥቆማዎች ሊደርሱ በማይችሉበት ሁኔታ ይሄን ያህል መጠን መጠቀሱ በራሱ አስደንጋጭ ነው ብለዋል። ከሕጻናት በተጨማሪም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
ወይዘሮ አልማዝ ጨምረው እንደገለጹት ከተደፈሩት ሴት ህፃናት በተጨማሪ 57 የሚደርሱ አብዛኞቹ እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ‘ወንድ ልጆች’ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
“የ14 እና የ17 ዓመት ልጆች በአባቶቻቸው ተደፍረዋል” – ወይዘሮ ማኅሌት ኃይለማርያም
የኢትዮጵያ ሴቶች መጠለያ ጥምረት ም/ሰብሳቢ ወይዘሮ ማኅሌት ኃይለማርያም ‘ከዋልታ ቴሌቪዥን’ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶችና ሕጻናትን የሚቀበሉ መደበኛ መጠለያዎች በኮሮና ምክንያት አዳዲስ ኬዞችን መቀበል በማቆማቸው በርካታ ዜጎች ተቸግረው እንደነበር ገልጸዋል።
አሁን ላይ አዲስ ኬዞችን የሚቀበል ለስድስት ወር የሚቆይ መጠለያ በቅርቡ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በመጠለያውም እስከ አሁን 27 የሚደርሱ በጾታዊ ጥቃት ፣ በአስገድዶ መድፈር፣ ልጅ በመካድና በባላቸው ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሚስቶች ተቀብሎ እያስተናገደ ነው ብለዋል።
በማዕከሉ ከገቡ ሕጻናት ውስጥ በአባቶቻቸው የተደፈሩ የ14 እና የ17 ዓመት ልጆችን እንደምሳሌነት የጠቀሱት ሰብሳቢዋ ላላስፈላጊ ውርጃ ተጋልጠው ሽንታቸውን መቆጣጠር የማይችሉበት ደረጃ ደርሰው ነበር ብለዋል።
በተለይ የ17 ዓመቷ ልጅ አባትየው የአደንዛዥ እፅ ጭምር እንድትጠቀም ማድረጉን ገልጸዋል። ጥቃቶች አይነትና መልካቸውን እየቀየሩ መምጣታቸውንም ነው የተናገሩት።
Source TIKVAH-ETH (Tsegab Wolde)
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!