የኢኒሺየቲቭ አፍሪካ ማህበር አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደ

ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኢኒሺየቲቭ አፍሪካ ማህበር አመታዊ ጠቅላላ ጉኤውን በካሶፒያ ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሄደ፡፡

ማህበሩ እ.ኤ.አ በ2023 ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በኢኖቬቲቭ ግራንት ፈንድ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩት የንግድ ዘርፍ ማህበራት እና የቢዝነስ ድርጅቶች አባላትን ማብቃት እንዲሁም ንግድ ለሰላምና ልማት እና ንቁ ዜጋ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተጨማሪም 17ኛ አዲስ አለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ፕሮግራሞች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ማህበሩ በዚሁ ዓመት በዋነኛነት ካጋጠሙት ችግሮች መካከል ለተለያዩ ለጋሾች ያቀረባቸው የድጋፍ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ አለማግኘቱ ነው ተብሏል፡፡ 

ማህበሩ እ.ኤ.አ በ2024 ካቀዳቸው ስራዎች መካከል ንግድ ለሰላምና ልማት፣ በብሔራዊ ደረጃ የበጎ ፈቃደኞች አገልግሎት እና በጦርነት ምክንያት በትምህርት ወደኋላ የቀሩ ልጃገረዶች የተፋጠነ ትምህርት እንዲያገኙ ማስቻል ፕሮግራሞችና 18ኛው አዲስ አለም አቀፍ ፊልም ፌሰቲቫልን ማካሄድ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሌላው በጉባኤው ላይ የቀረበው የማህበሩ እ.ኤ.አ የ2023 የኦዲት ሪፖርት በውጭ ኦዲተር አማካኝነት ሲሆን ማህበሩ በዚህ አመት ከለጋሾች ያገኘውን ድጋፍ 87 በመቶ ለፕሮግራም 13በመቶውን ደግሞ ለአስተዳደራዊ ወጪ መዋሉን በግልጽ ተብራርቷል፡፡ በዚህም አሉ የውጭ ኦዲተሩ ማህበሩ ያለፈው አመት የሥራ ክንውኑ የአለምና የሀገር አቀፍ የፋይናንስና የአስተዳደር ደንብና ስርዓት ጠብቆ ማከናወኑ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የማህበሩ የጠቅላላ ጉባኤ አባላትም የቀረበላቸው የሥራ ክንውንና የኦዲት ሪፖርት እንዲሁም የዚህ አመት የሥራ እቅድ ላይ ተወያይተው ሁሉንም ሪፖርቶች በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ መሰረት ኢኒሺየቲቭ አፍሪካ ጊዜውን ጠብቆ አመታዊ ሪፖርቶችን እና እቅዶችን እንዲሁም ደጋፊ መረጃዎችን አሟልቶ ማቅረቡን የባለስልጣኑ መ/ቤት ማረጋገጫ መስጠቱ ታውቋል፡፡    

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *