ጩህ ጩህ አለኝ

                                                                            አያሌው አስረስ 

                                                                             (ለኢኒሺየተቭ አፍሪካ የቀረበ)

          መስቀል አደባባይ አጠገብ በሚገኘው አዲስ አበባ ሙዝየም ውስጥ ሰሞኑን አንድ አውደ ትርኢት ቀርቦ ነበር፡፡ አውደ ትርኢቱን ያዘጋጁት ሴታዊት የሚባል መንግሥተዊ ያልሆነ ድርጅት, ከዩኔ ውመን እና የስዊዲን ኤምባሲ (Sweden Embassy) በጋራ በመሆን ነው፡፡ ‹‹ ምን ለብሳ ነበር? ›› በሚል ርእስ የቀረበው ይህ አውደ ርእይ ያተኮረው አለባበስን ተንተርሶ  በሴቶች ልጆች ላይ የተፈጸመውን የወሲብ ጥቃት በማሳየት ላይ ነው፡፡እኛ ደግሞ  ጾታ እንጂ አለባበስ የመደፈር ምክንያት አይደለም፤ ያ ቢሆን  ኑሮማ  የአለቀ የተማሪ የደምብ ልብስ (ዩኒፎርም )  የለበሰቸው  መክሊት በምን ምክንያት ትደፈራለች? ብለን እንሞግታለን:: ፊት ለፊት አያምጡት እንጂ የእነሱም መሻት ይህን መስረገጥ ነው፡፡

ጥቃቱ የተፈጸመባቸውን ልጆች በእድሜ  ስናይ  ደግሞ የሰባት አመቷን አሚናን  እና የአስራ ዘጠኝ አመቷን መንበረን እናገኛልን፡፡ጥቃቱ የደረሰባቸው 16 ሴቶች ሲሆኑ ጥቃት አድራሽ ወንዶች ደግሞ 17 ናቸው፡፡ ይህ ማለት አንደኛዋ በሁለት ወንዶች ተደፍራለች ማለት ነው፡፡ ጥቀቱን ከፈጸሙት 17 ወንዶች ለሕግ የቀረቡት ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ በሕግ ቁጥጥር ሥር ገብቶ የነበርው ሶስተኛው አጥቂ ለፖሊስ ጉቦ ሰጥቶ መውጣቱና መልሶም አለመያዙ ተገልጧል፡፡ አራተኛው ደግሞ በዋስ ወጥቶ በዚያው ጠፍቷል፡፡

የመደፈር አደጋ ከደረሰባቸው ውስጥ አንዷ  ኮከብ የተደፈረቸው ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ነው፤እስረኛ ሆና ተገኝታ  አይደለም ሕግ የጠብቀኛል ብላ ገብታ እንጂ፡፡  ከታሪኩ የድርጊቱን አፈጻጻም መገመት ይቻላል፡፡ ኮከብ  ከመኖሪያዋ ብዙም ወደ ማታውቀው አካባቢ ርቃ   ሔዳለች፡፡ ልትመለስ ስታሰብ ጊዜው መሽቷል፡፡ በዚያ የምታውቀው ያሳድረኛል የምትለው  ሰው ወይም ዘመድ የላትም፡፡ ስለዚህም ፖሊስ ጣቢያ ተጠግታ አድራ በሰላም ወደ አካበቢዋ ለመመለስ ወስና ጣቢያ ትሔዳለች፡፡ በቦታው የነበሩት ፖሊሶች በሃሰቧ ተስማምተው ከሴት እስረኞች ጋር እንድታድርና ጠዋት ወደ አገሯ እንድትሔድ  ይወሰናሉ፡፡ ተረኛ ፖሊሱ ግን ወስዶ ከሴት  እስረኞች ጋር እንድታድር አላደረገም፡፡ ከእረሱ ጋር እንድታድር አድርጎ ደፈራት፡፡ ጠዋት ላይ ወስዶ ከሴት እስረኞች ጋር ሲቀላቅላት እስረኞች ተቀወሙ፡፡ ስለዚህም ወንጀሉ ተጋለጠ፡፡ ምን ያደርጋል እሱም ለሕግ አልቀረበም፡፡ጩህ ጩህ የአለኝ ለዚህ  ነው፡፡

በአክሰትና ባጎት እጅ አድገው ለቁም ነገር የደረሱ ብዙዎች ቢኖሩም የቤዛዊት እጣ ግን ያማል፡፡ ‹‹ መጣችልህ የፈለግከውን አድረጋት›› ብላ አሳለፋ ለደፋሪው የሰጠቻት ወገኔ ብላ የተጠጋቻት  እንደ አንድ የቤት ሠራተኛ አገልጋይዋ አድርጋ ጉለበቷን ሰትበዘብዛት የነበረችው  አክስቷ ናት፡፡   የሰባት አመቷ የአሚና እና የአስራ ስምነት አመቷ የአርሴማ ጥቃት ደግሞ ለመናገር እራሱ ይከብዳል፡፡ ሰው ከሰውነት ወርዶ ፍጹም እንስሳ ሆኖ በእንስሳነት በሕሪውና ተግባሩ የተገለጠበት ድርጊት ነው፡፡ አርሞ ኮትኩቶ ለቁም ነገር ማድረስ የነበረበትን አባት  የገዛ ልጁን ሲደፍር  በምን ቃል ምሬትንና ጥላቻን  መግለጥ ይቻላል ? የክርሰትናና የእስልምና ወይም የሌላ እምነት ተከታይ ሃይማኖተኛ ሕዝቦች ነን  የምንል ሰዎች  የሞራል ልዕልናችን ወደ የት አለ?  ብሎ መጠየቅ ግድ ይሆናል፡፡ይህ አይነቱ ቅሌትና የሞራል ዝቅጠት አያሰጮህም?

በመጠቃተቸው የደረሰባቸው ጉዳት ሳያንሰ አንዳንዶቹ ለማርገዝና ለመውለድ ተገድደዋል፡፡አክስቷ ለመደፈር የዳረገቻት ቤዛዊት ልጇን ለማየት ምን ያህል ትጠላ እንደነበር የምተናገረው ምርር ባለ ቃል ነው፡፡ መከራውንና የመከራውን ማስተወሻ በአንድነት ለመያዝ መገደድ እሷን አታድርገኝ ያሰኛል፡፡

ጥፋቱ እንደተራ ጉደይ ታይቶ ፋይሉ የትም ተጥሎ ይሆናል፡፡ ተበዳዮች ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተመላልሰው ነገሩን ለመቀስቀስ ሲነሱ ምን እንደሚጠብቀቸው ኤተወቅም፡፡ ምን አልባት  መጠቋቆሚያም እየተደረጉ እየተሸማቀቁ ተጨማሪ ጉዳት ላለማስተናገድ ቢቀርስ ብለው ነገሩን ትተውት ሸሽተው  ቤታቸው ገብተው ዘግተውም  ይሆናል፡፡መጮህ አሁንም መጮህ የሚያስፈልገው በሕገ አስፈጻሚው ላይ ነው ፡፡ ‘እነእከሌ ምን ሆኑ’ የሚሉ ተጨማሪ ጥቃት ፈጻሚዎች እያበዛብን እንዳይሆን ያሰጋል። ሁሉም ወገን በህፃናትና ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ለመከላከል ዘብ ሊቆም ይገባል። በተለይ በት/ቤቶችና በማህበረሰቡ ውስጥ የባህርይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ከተቋቋሙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር መተባበር ያስፈልጋል።

1 reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *