የኢንሼቲቪ አፍሪካ ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አካል የሆነው ኢንሼቲቭ አፍሪካ አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን  መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም በሞዛይክ ሆቴል ተካሄዷል፡፡

ድርጅቱ እ.ኤ.አ በ 2020 ያከናወናቸው ስራዎች በሶስት መርሃ ግብሮች የተከፋፈሉ ሲሆን እነዚህም “ለውጥ በለውጥ – የስርዓተ ፆታ ጉዳዮችን ማካተት፣ በአካባቢ ልማት የወጣቶችን ልማት ማሳደግ እና የዜጎች ትምህርት እና  የምርጫ ጉዳዮች እንዲሁም የንግድ ዘርፍ ማህበራት እና ምክር ቤቶችን መደገፍ እና አቅም ማጎልበት በተጨማሪም  14ኛው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ስራዎች እንደሆኑ የድርጅቱ ጊዜያዊ ሥራ አስኪያጅ አቶ የኋላሸት ገ/ሚካኤል ካቀረቡት ማብራሪያ መረዳት ተችሏል፡፡

ድርጅቱም በዚህ አመት ያጋጠሙት ችግሮች እና የተወሰዱ እርምጃዎችን  ጊዜያዊ ሥራ አስኪያጁ ለጉባኤው አባላት ሲገልፁም  ከመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሀገራችን በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ እና እርሱን ተከትሎ የተወሰደው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስብሰባን እና ተቀራርቦ መስራትን መከልከሉ የታቀዱ ተግባራት በመጓተታቸው ይህንንም ከድጋፍ ሰጪዎች ጋር በመነጋገር የእቅድ ክለሳ መደረጉን  ጠቅሰዋል፡፡

አቶ የኋላሸት በማያያዝም ድርጅቱ ዓላማውን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት እንዲያስችለው ለተለያዩ ለጋሾች ያቀረበው የፕሮጀክት ፕሮፖዛል አዎንታዊ ምላሽ  አለማግኘቱንም እንደችግር  አስቀምጠዋል፡፡

ድርጅቱ እ.ኤ.አ በ2020 ላከናወናቸው ተግባራት በአጠቃላይ ከብር  18 ሚሊዮን  932 ሺህ ብር በላይ ወጪ ማድረጉን  በውጭ ኦዲተር የተረጋገጠ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የፕሮግራም ወጪ 84 በመቶ፣ የአስተዳደራዊ ወጪ ደግሞ 16 በመቶ መሆኑን ከውጭ ኦዲተሩ ሪፖርት ማወቅ ተችሏል፡፡

ኢንሼቲቭ አፍሪካ እ.ኤ.አ በ2021 ዐም ያቀዳቸው ፕሮግራሞች የድርጅቱ  ጊዜያዊ ስራ አስኪያጅ በዝርዝር  ለማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ  አባላት  የገለፁ ሲሆን  ከእነኚህም መካከል  እ.ኤ.አ በ 2020 ያልተጠናቀቁትን ማጠናቀቅ በ ”ለውጥ በለውጥ – 2 የንግድ ማህበረሰብ  ለሰላም” እና የዜጎች ትምህርት ጉዳዮች እንዲሁም  በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ  የመጀመሪያ ጊዜ መራጮች ትምህርት በተመረጡ  ሁለተኛ ደረጃ  እና ዩኒቨርሲቲዎች መስጠት በተጨማሪም  በተመረጡ ጉዳዮች የተለያዩ የውይይት መድረኮችን  በማዘጋጀት ማወያየትም ሌላው የፕሮግራም ተግባር መሆኑ ታውቋል፡፡

የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት በቀረቡላቸው ሪፖርቶች እና እቅዶች ላይ አንዳንድ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ከጠየቁ በኋላ ባገኙት ምላሽ ረክተው  ሪፖርቶቹን መሉ በሙሉ  ተቀብለው አፅድቀዋል፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *