ሰላም ለንግዱ ዘርፍ ለአገር ግንባታ ወሳኝ ነው 

ከእሸቱ ደስታ  

ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ አስፈላጊ እና ዋነኛ ከሆኑ እሴቶች አንዱ ነው፡፡ በማንኛውም መልኩ እጅግ በጣም ጠቃሚ አይደለም የሚባል ሰላም እንኳ ፍትሐዊ ነው ከሚባል ጦርነት ይመረጣል፡፡ ሰላም ከሁሉም ፍትሕ ይበልጣል፡፡ የጦርነት ጥሩም ሆነ መጥፎም የለም፡፡ ሰላም የሁከት እና የብጥብጥ ተቃራኒ ነው፡፡ ሰላምን ብዙዎች ከስጋት ነጻ መሆን፣ አለመረበሽ፣ መረጋጋት፣ ነፃነት ብለው ይገልጹታል፡፡  

ለዚህም በአገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግጭቶች ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የተለያየ ባሕሪ በመያዝ በተደጋጋሚ እየተከሰተ መሆኑን ከፍተኛ እና አሳሳቢ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እያስከተለ ይገኛል፡፡ በግጭቶች ሳቢያ በርካታ ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ ተሰደዋል፡፡ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ማህበራዊ ግንኙነቶች ተዛብተዋል፡፡ ይህንን አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን አደጋ እና ስጋት መመልከት ለሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ አንገብጋቢ እና ተቀዳሚ አጀንዳ ሆኗል፡፡  

ይህ ሁኔታ እልባት እንዲያገኝ ከሚፈልጉት የሲቪል ማህበረሰብ  ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኢኒሼቲቭ አፍሪካ ከሚያከናውናቸው በርካታ ተግባራት መካከል በሰላም ግንባታ ዙሪያ ኘሮጀክት ቀርጾ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑ ነው፡፡  

በዚህም በተለይ ንግድ ለሰላም እና ልማት በሚለው ኘሮግራሙ የንግዱ ዘርፍ ተዋንያኖች በተለያዩ የግጭት ቀጠናዎች ውስጥ መደበኛ የንግድ ስራቸውን የመቀጠል እና ከሌሎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ በመስራት ማህበረሰቡ ለረጅም ጊዜ እርስ በርስ ተከባብሮበት የኖረው ማህበራዊ ሰንሰለት እና የአብሮነት ውል ሳይበጠስ እንዲቀጥል በማገዝ ረገድ ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ያምናል፡፡  

ይህም ብቻ አይደለም የግሉ ዘርፍ የስራ እድሎችን በመፍጠር፣ ለሰላም መደፍረስ የተጋለጡ  አካባቢዎችን እንዲያገግሙ በማገዝ ብሎም ወደ ዘላቂ ሰላም የሚያመሩበትን መንገድ በመፍጠርም ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡  

በዚህም ንግድ ለሰላም ኘሮግራም ትኩረት ሰጥቶ በዋናነት እየሰራባቸው ካሉት ቁልፍ ተግባራት አንዱ የግሉን ዘርፍ አቅም መገንባት ላይ ነው፡፡ ከአቅም ግንባታ በተያያዘ የንግዱ ማህበረሰብ ወይም የግሉ ዘርፍ በአገራዊ ምክክሩ አገራዊ መግባባት እና በሰላም ግንባታ ዙሪያ የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንዲችል የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ሰጥቷል እየሰጠም ይገኛል፡፡  

ከዚህ በመነሳትም የንግዱ/የግሉ ዘርፍ በአገራዊ ምክክሩ ሚናቸው ጐልቶ እንዲወጣም እየተሰራ ነው፡፡ በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በአገራችን ከሚገኙ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት፣ የነጋዴ ሴቶች ማህበራት እንዲሁም ከቢዝነስ አባል ድርጅቶች ጋር በተደረጉ ምክክሮች በአጀንዳነት እንዲቀርቡ የሚነሱ ነጥቦች አሉ፡፡  

በቅድሚያ የንግድ ሥራ በተሟላ ሁኔታ ለማከናወን የሚያስፈልገው ወጪ እንዲቀንስ መንግስት ታክስን እና የተለያዩ ክፍያዎችን መቀነስ እና ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል፣ በፖለቲካ ያለመረጋጋት እና በአካባቢ አስተዳደሮች በንግዱ/ በግሉ ዘርፍ በሚገኙ ማህበረሰቦች ላይ የሚፈጸሙ ተጽእኖ እንዲሁም የክልል ተወላጆች አይደላችሁም በሚል ማግለል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መወያየት አስፈላጊ መሆኑን በተጨማሪም የግሉን/ የንግዱን ዘርፍ ከማጠናከር አኳያ ምክክሩ በግሉ ዘርፍ የሚመራ እድገትን ማበረታታት እና ንግድ ሥራ ማከናወን ምቹ ከባቢን መፍጠር ይገኝበታል፡፡  

በሌላም በኩል በሞኖፖል አሰራሮች ላይ እርምጃ መውሰድን፣ ስራ ፈጣሪነትን እና ለሁሉም ገበያ እና ተዋንያን እኩል የመወዳደሪያ  ሚና መፍጠሩን ተጠቃሽ ነው፡፡ ሌላው ለግሉ ዘርፍ የንግድ ፖሊሲዎችን እና ደንቦች ለማሳያ የንግድ፣ የትራንስፖርት፣ የገቢ እና ወጪ እንዲሁም የታክስ እና የጉምሩክ ፖሊሲዎች እና ደንቦች ላይ ትኩረት መስጠት እንዲሁም ከግሉ/ንግዱ ዘርፍ ፍላጐት ጋር የተጣጣመ እና ምርታማነትና ፈጠራን የሚያጐለብት የትምህርት ኘሮግራም ማስፋፋት፣ የሰራተኛ ዜጋው ክህሎት እንዲበለጽግ በቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ያተኮረ የትምህርት መርሃ ግብር ላይ በስፋት መዋዕለ ነዋይ እንዲፈስ እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል፡፡  

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *