ግጭትን ለማስወገድ የመቻቻል ባህልን ማጠናከር ያስፈልጋል
ከእሸቱ ደስታ
በሐገራችን ግጭቶች ብዙውን ጊዜ ምንጫቸው ሌላውን ሰው ወይም ሌላውን ወገን በስህተት መሳል ነው፡፡ ይህም ስለሌላው ያለን እይታ የተዛባ የግጭት ምንጭ ሲሆን እናየዋለን፡፡ ይህንንም በጥቂቱ እንመልከት በሐይማኖት ረገድ አንድ እስላም ወይም ክርስቲያን የሆነ ሰው ሌላውን የሚያይበት እይታ የተዛባ እና ትክክል አለመሆኑ፣ አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ አይነት አመለካከት በብሔረሰብ ውስጥም ይንጸባረቃል፡፡ ይህም ጠባብ የፖለቲካ ስሜት ያለው አንድ ኦሮሞ ስለ አማራው ወይም አማራው ስለ ኦሮሞው ወይም ጉራጌው ስለ ትግሬው ወዘተ በአእምሮው ይዞት ስሎት ያለው ስዕል ልክ ያለመሆኑን ያጋጥማል፡፡
ሌላው ስልጣን ነው፡፡ ስልጣን ዓለምን እያፋጀ ያለ ነገር ነው፡፡ በስልጣን ዙሪያ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚጣሉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በመሳፍንት ዘመን “እኔ” የሰለሞን ዘር በመሆኔ ስልጣን ይገባኛል፡፡ ንጉስ መሆን አለብኝ የሚለው በአንድ ወገን በአጋጣሚ ሰብሮ የሚወጣው በሌላው ወገን በሚያደርጉት ሽኩቻ ሕዝቡን ያፋጁበት ጊዜ ቀላል አይደለም፡፡ በደረግ ዘመንም በፖለቲካ ሽኩቻ ወገን እርስ በርሱ የተላለቀበትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሀፓ) እና የመሳሰሉት ሕዝቡን ለእልቂት ዳርገውታል፡፡ ሌላው ኢኮኖሚ ነው፡፡ አንዳንዱ አካባቢ ለም እና በቂ ሀብት አለው፡፡ ሌላው ደግሞ የለውም፡፡ በዚህ መነሻ ሰው በተፈጥሮው ለም እና ሐብት ወዳለበት አካባቢ ይሰፍራል፣ ይሰማራል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን አንዳንድ ግጭት ፈጣሪዎች በሰፋሪዎቹ ላይ ጠብ በመጫር ከአካባቢው እንዲለቁላቸው የሚጥሩ አልጠፉም፡፡ እንግዲህ እነዚህ አጓጉል እና ትክክል ያልሆኑ በአእምሮአችን ስለን የምናስቀምጣቸው ነገሮች የግጭት ምንጭ ይሆናሉ፡፡ እንዲህ አይነቱ ነገሮችን አዛበተን የማየት እና በትክክለኛ መልካቸው ያለማስቀመጥ ባሕል ሊወገድ ይገባል፡፡
ግጭት ባለበት ሀገር ሰብዓዊ መብት እና የንብረት ጥበቃ ብሎ ነገር የለም፡፡ ሕዝቡ እንዲሁ እንደደማ፣ እንደተዘረፈ ነው የሚኖረው ለማሳያ ያህል ግጭት ያስከተለው ጉዳት አለፍ አለፍ ብለን ለመቃኘት እንሞክር፡፡ ንጉስ ኢዛና “እኔ” ይላል፡፡ “ከተከዜ ማዶ ሱዳን፣ ቤንች፣ ምጵዋ፣ ራያ እና ዘቦ አካባቢ ያሉ ሰዎችን ወግቼ ንብረታቸውን ዘርፌ መጣሁ” ይል ነበር፡፡ ዮዲት ጉዲት በዘመነ መንግስቷ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አቃጥላ፣ አክሱምን አፍርሳ፣ የነበረውን የመንግስት ተቋማት በሙሉ ድራሹን አጥፍታለች፡፡ በአጼ ኃ/ሥላሴ ዘመን መንግስት ደግሞ አንጻራዊ ሰላም አለ ቢባልም የኢርትራ ነፃነት ግንባር፣ የትግራይ፣ የጐጃም፣ የባሌ እና የደራሳ ሕዝብ ንቅናቄ በመኖሩ ምክንያት በግጭቶቹ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በደርግ ሕዝቡ በአዋጅ እና ያለ አዋጅ ንብረቱ ተቀምቷል የኤርትራ ነፃነት ግንባር እና የሕውኃት ጦርነት እንዲሁም በውስጥ በተፈጠረ የፖለቲካ ድርጅቶች ሽኩቻ ሐገሪቱ ደም በደም ተራጭታለች፡፡ በዘመነ ኢሀዲግም ሆነ አሁን በፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት በተለይ በአማራ፣ በትግራይ እና በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ወገኖች የሚደርስባቸው ፈተና ተገልጾ አያበቃም፡፡ በዚህም በርካቶች ተገለዋል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል ወይም ተሰደዋል፡፡ ንብረታቸውም ቢሆን ተቃጥሏል ተዘርፏል፡፡ ይህም እስከ አሁን የሚታይ ክስተት ሲሆን የሁሉንም ወገን ለሰላም ርብርብን ይጠይቃል፡፡
ሌላው በሀገራችን ባህላዊ የግጭት አፈታት የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ሲሆን ከዚህም ውስጥ በሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን በማምጣት በኩል ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በኦሮሞ ባህል በሽምግልና የሚቀመጥው አባ ገዳ ይመስለኛል፡፡ ቤቱ አጥር የለውም አይዘጋም በአጠቃላይ ሁሉም ነገር በቤቱ አጥር ውስጥ የተሟላ ነው ማንም ደኝነት የፈለገ ሰው ሰተት ብሎ ነው የሚገባው እሱ ካለ፣ ከተናገረው፣ ከፈረደው ውጪ እልፍ ማለት አይቻልም አሁን አሁን እየላላ ሄደ እንጂ በጉራጌም እንደዚሁ ነው፡፡ ጉራጌ “ቅጫ” የሚል ሕግ አለው፡፡ ይሄ ቅጫ እንደ ሕገ መንግስት ማለት ነው፡፡ በዚህም መነሻ ማንም ሰው ሰው ገድሎ ወይም ንብረት ዘርፎ በሰላም ሊቀመጥ አይችልም፡፡ በሆነ ምክንያት ሰው የገደለ ከሆነ እርሱን በደም አይበቀለውም፡፡ ግድያን በግድያማ ከጨረስከው ያው መቆሚያ የለውም፡፡
ስለዚህ የገደለ ሰው ለሟች ቤተሰብ የገንዘብ ካሳ ይከፍላል፡፡ ይህንንም ገንዘብ ገዳይ ብቻ ሳይሆን ጐሳውም ያዋጣል፡፡ ይሄ በዚህ ብቻ አይቆምም የገዳይ እና የሟች ሚስት ልጆች ይጋባሉ፡፡ የንብረት ዘረፋ ካጋጠመ ደግሞ የተዘረፈው ሰውዬ ንብረት ሙሉ በሙሉ እንዲመለስ ይደረጋል፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን የሽማግሌው ስርአት እኮ ነው ይዞ አገሩ ያቆየው፡፡
በባሕላዊ የግጭት አፈታት ጊዜ ከዘመናዊ ጋር ተቀናጅቶ መቀጠል አለበት፡፡ በዚህም በባሕልም ሕግ ነገር ለማጣራት ብዙ ጊዜ ይፈጃል፡፡ ይህ ማጠር አለበት፡፡ ለዚህም ባሕላዊውን ከዘመናዊ ሕጐች ጋር በማስማማት እና በማዋሀድ ለአገር ሽማግሌዎችም ሆነ ለሀይማኖት አባቶች ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ሌላው ሽማግሌዎች ስንል አሁን ያሉት ሽማግሌዎች ጊዜውን ጠብቀው አይኖሩም፣ይሞታሉ፡፡ የተማረ ሰው ከስር ከስሩ መተካት አለበት፡፡ የተማረው ሰው የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባሕል፣ ሐይማኖት እና ስርአት ጠንቅቆ ማወቅ እና መማር ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ሲሆን የሀገር ሽማግሌዎች ስርአት ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል፡፡ በግጭት ዙሪያም የሚከሰቱ ችግሮችም እንዲሁ ደረጃ በደረጃ ይፈታሉ፡፡
የግጭት አፈታት እና አወጋገድን ስኬታማ ለማድረግ መንግስትን ጨምሮ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከሕዝቡ የሚጠበቁ ዋነኛ ተግባራት በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡
መንግስትን በተመለከተ፡- የሀገራችን ሰው መንግስት እና ፀሐይ አንድ ናቸው ይላል፡፡ ይህም ሁለቱም ሲያበሩ ለሁሉም በእኩልነት መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በመንግስት በኩል ብርሐኑ ለሁሉም ዜጋው እኩል ካልሆነ ግን ጥርጣሬ ያሰነሳል፡፡ ተአማኒነቱም ይቀንሳል፡፡ ሌላው ለአንድ ሀገር መንግስት የሕዝብ ተቀዳሚ አባት እና ሐብት ስለሆነ ይህንን ባሕሪ ማጣት የለበትም፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን ደግሞ መንግስት ሕግ ያወጣል፡፡ የሚያወጣቸውንም ሕጐች ለሕዝቡ የሚጠቅሙ፣ የሚያሳድጉ፣ የሚያሰሩ መሆን አለባቸው፡፡ ከዚህ አኳያ መንግስት ያወጣውን እራሱ መጠበቅ አለበት፡፡ ይሄ ካልሆነ የመንግስትነት ባሕሪውን ያጣል፡፡ በተጨማሪ መንግስት የፍትሕ አባት ነው ሕዝብ ሌላ መሸሻ የለውም፡፡ ፍትሕ የመንግስት ጥብጣብ ናቸዋ እና ፍትሕ ሊያጓድል አይችልም፡፡ ስለሆነም ፍትሕን በማስተናገድ ሕዝብ ከመንግስት ብዙ ይጠብቃል፡፡ መንግስት ደግሞ የፍትሕ አባትነቱን ማረጋገጥ ግዴታው ነው፡፡ ይህ ሲሟላ ብቻ ነው የግጭት መንስኤዎች የሚደፈኑት፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በተመለከተ፡- ዩኒቨርስቲ ማለት ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተለያየ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ስልጣኔ ያላቸው ወገኖች ተሰባስበው አንድ ቦታ የሚገናኙበት መናሃሪያ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰላም፣ የመግባቢያ፣ የመወያያ በአጠቃላይ ወጣቶችን በእውቀት የመቅረጽ ኃላፊነት የተጣለባቸው ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት ዩኒቨርስቲዎች በካሪኩለማቸው ውስጥ የግጭት መከላከልን ጉዳይ ትልቅ ቦታ ሊሰጡት ይገባል፡፡ በእርግጥ ጅምሩ ያለ ቢሆንም ተጠናከሮ መቀጠል አለበት፡፡ ይህ ተግባራዊ ሲሆን ነው፡፡ የሰላም ጀግኖችን በብዛት ማፍራት የምንችለው፡፡ ይሄ ሐሳብ በኢትዮጵያ በግጭት መከላከል ዙሪያ ዩኒቨርስቲ መቋቋም አለበት፡፡ ይህም ተግባራዊ እንዲሁን የሚመለከታቸው ሁሉ በጋራ ሊያስቡበት ይገባል፡፡
ሕዝቡን በተመለከተ፡- ሕዝቡ የግጭት መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ወዲያው ለማስወገድ እርስ በርስ የመነጋገር፣ ተቻችሎ የመኖር ባሕልን ማዳበር ያስፈልገዋል፡፡ እንዲሁም መንግስትን በዚህ ረገድ የማገዝ፣ በትክክለኛ አቅጣጫ የማይጓዙትን የመንግስት ኃላፊዎችንም ሆነ ሌሎችን የመቆጣጠር እና የማጋለጥ ትልቅ ሚና አለው፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!